ስጦታ ምንድን ነው?
የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም
በስጦታ እና በውርስ መካከል ያለውን ልዩነት እና አንድነት ያውቃሉ? በኵር ጉዳዩን አስመልክቶ በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የፍትሐብሔር ጉዳዮች አቃቢ ሕግ ባለሙያ አቶ እንደግ ሰውነትን አነጋግራለች:: የዘርፉ ባለሙያ እንዳብራሩት ስጦታ ማለት በፍትሐብሔር ሕጉ በአንቀጽ 2427 በተሰጠው ትርጉም መሠረት ስጦታ ሰጭው ለስጦታ ተቀባዩ ችሮታ በማድረግ ከንብረቶቹ አንዱን ወይም ሁሉን የሚሰጥበት ወይም ግዴታ የሚገባበት ውል ነው::
ከንብረቶቹ የሚለው ቃል ስጦታ ሰጭው በሚሰጠው ንብረት ላይ ስጦታ ተቀባዩ የባለቤትነት መብት አለው:: ከዚህ በተጨማሪ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2451 ድንጋጌ ሲታይ በስጦታ የሚሰጠው ንብረት ስጦታው በተደረገበት ቀን የስጦታ ሰጭው ገንዘብ ከሆነው ንብረት ላይ ብቻ ነው በማለት መደንገጉም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው::
የስጦታ ውሉ በሕግ ፊት የሚጸናው በፍትሐብሔር ሕግ 1678 መሠረት፦
ውል ለማዋዋል ችሎታ ባላቸው ሰዎች ሲፈፀም፣
በቂ የሆነ ፣መረጃ ያለው( እዉነተኛ የሆነ) ፣ የሚቻል እና ሕጋዊ ጉዳይ መሆኑ ፣
የውሉ አጻጻፍ (አይነት) በሕግ የታዘዘ መሆኑ ተረጋግጦ ሲፈፀም ነው::
አንቀጽ 834 እና 836 ስለስጦታ ማድረግ እና መቀበል፣ ስጦታን ማድረግም ሆነ ስጦታን ተቀብያለሁ ለማለት የሚችለው ራሱ ወይም ሕጋዊ ወኪሉ ነው:: አንቀጽ 2430 ያለዋጋ የሚሆን አገልግሎት፣ ያለዋጋ ሥራ መሥራት ወይም ያለዋጋ እቃ ለሌላ ሰው ማዋስ ስጦታ አይባልም ሲል አስቀምጦታል::
አንቀጽ 2435 የተስፋ ቃል መስጠት ወይም ስጦታ አደርጋለሁ ብሎ የተስፋ ቃል መስጠት የግድ የመስጠት ግዴታን አያስከትልም:: ነገር ግን ቃል የተሰጠው ሰው በተሰጠው ቃል ምክንያት በቅን ልቦና ጉዳይ ለመፈፀም ያወጣው ገንዘብ ካለ እንዲመለስለት ብቻ በሕግ የመጠየቅ መብት አለው::
የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 2458 ስጦታ ተቀባይ ለስጦታ ሰጭ ቀለብ የመስጠት ግዴታ በግልጽ የተነገረ የውል ቃል ባይኖርም እንኳን ሰጭው በድህነት ላይ ወድቆ ሲገኝ ስጦታ ተቀባዩ ቀለብ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ያስገድዳል::
የስጦታ እና የኑዛዜ አንድነት እና ልዩነት
የስጦታ እና የኑዛዜ ውርስ አንድነት(ተመሳሳይነት) ሁለቱም አንድ ሰው የራሱን ንብረት ራሱ ወዶና ፈቅዶ ያለማንም አስገዳጅነት ለሌላ ሰው የሚያስተላልፍባቸው መንገዶች መሆናቸው ፣ ሁለቱም ተግባራት በነጻ ያለምንም የዋጋ ችሮታ የሚፈጸሙ መሆናቸው፣ ሁለቱም በፆታ ምክንያት ልዩነት የማያደርጉ መሆናቸ፣ በሁለቱም (ኑዛዜም ሆነ ስጦታ) መኖሩን የማስረዳት ግዴታ የተጠቃሚዎች መሆኑ በፍትሐብሔር ሕጉ 896 እና 2447 ተመላክቷል::
በሁለቱም ገደብ ወይም ግዴታ መጣሉን በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 916 መሰረት ተፈጻሚ ይሆናል:: ኑዛዜው አንድ ሁኔታ ሲደርስ የሚጸኑ ወይም የሚቀየሩ ሆነው ሊደረጉ የሚችል እና በ2455 ስጦታ ተቀባይ የመጦር ግዴታ ገደብ ሊደረግ ይችላል::
የስጦታ እና የውርስ ልዩነት
ስጦታ ሰጭው በሕይወት እያለ ንብረቱን ለስጦታ ተቀባዩ እንዲተላለፍ የሚፈጽመው ተግባር ነው:: ውርስ ደግሞ አውራሽ ከሞተ በኋላ ንብረቱ ከአውራሽ ወደ ሕጋዊ ወራሽ የሚተላለፍበት መንገድ መሆኑን አቶ እንደግ አስረድተዋል::
የስጦታ እና የኑዛዜ ባለመብት ለመሆን ዝምድና የግድ አስፈላጊ አደለም:: ያለ ኑዛዜ የውርስ ባለመብት ለመሆን በዝምድና መተሳሰር አስፈላጊ እንደሆነ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 856 ተቀምጧል::
ስጦታ ማድረግም ሆነ ስጦታን ተቀብያለሁ ለማለት በውክልና እንደሚቻል በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 834 እና 836 ተቀምጧል:: የኑዛዜ ውርስን ግን በውክልና ማድረግ እንደማይቻል የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 857 ያስቀምጣል::
ስጦታ በሕግ ፊት የጸና ለመሆን በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2436 ንኡስ ቁጥር አንድ መሠረት የስጦታ ተቀባዩን ፈቃድ የሚጠይቅ ነው:: የኑዛዜ ውርስ በሕግ ፊት የጸና እንዲሆን ኑዛዜ በሚደረግበት ጊዜ ኑዛዜ ተቀባይ ፈቃዱን መስጠት አይጠበቅበትም:: ውርሱን ካልፈለገው ግን በሌላ ጌዜ ወራሽ መሆኑን አጣሪው ካሳወቀበት ቀን አንስቶ እስከ አንድ ወር ባለው ጊዜ ውርሱን አልፈልግም ማለት ይችላል ሲል በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 978 ተቀምጧል::
የይርጋ ጌዜ ገደብን በተመለከተ
ስጦታ የተደረገለት ሰው የስጦታ አፈፃጸሙን በምን ያህል ጌዜ ውስጥ መጠየቅ እንዳለበት የስጦታ ውልን በሚደነግገው የሕግ ክፍል የተቀመጠ የጊዜ ገደብ የለም:: ገደቡ ባይኖርም ግን ስጦታ ውል እንደመሆኑ ሊፈጸም የሚገባው በጠቅላላው የውል ሕግ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1676 ንኡስ ቁጥር አንድ እና 1845 ድንጋጌዎች መሠረት ነው:: በዚህም በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ስለመሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመታወቂያ ቁጥር 42691 አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠ ሲሆን በወራሾች መካከል የሚነሳ የውርስ ንብረት ክርክር በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1000 ንኡስ ቁጥር አንድ በተደነገገው አግባብ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ መቅረብ አለበት::
የሟች ወራሽ የሆነ ሰው ንብረቱን በያዘው ወራሽ በአልሆነው ሰው ላይ ክስ ማቅረብ የሚችለው ደግሞ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1845 መሠረት እስከ አስር ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያ አብራርተዋል::
( ማራኪ ሰውነት)
በኲር የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp://
www.ameco.et/Bekur በቴሌግራም -
https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።